“ጽዮን ማርያም ሰንበት ት/ቤት” በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው ሀገረ ስብከት በደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን  ውስጥ የሚገኝ ሲሆን  መስከረም 6፣ 2004 ዓ.ም በሰንበት ት/ቤት ደረጃ የተቋቋመበትን 1ኛ ዓመት ያከብራል።    በሰንበት ት/ቤት ደረጃ ከመቋቋሙ በፊት፣ ማኅበረ ጽዮን ማርያም በመባል ይጠራ ነበር። “ጽዮን ማርያም” የሚለውም ስያሜ ከዚያ የተወሰደ ነው።

  የማኅበረ ጽዮን ማርያም አመሠራረት

          ማኅበሩ በሁለት ወንድሞች ተጠንስሶ ከሳቴ ብርሃን ጉባኤ በሄዱ ስድስት ወንድሞች ነሐሴ 30 1997 ዓ.ም ተመሠረተ። በጊዜው ማኅበሩን ለመመሥረት ያስገደዱ ሁለት ዋና ምክንያቶች  በአካባቢያችን (በዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ) ምንም አይነት መንፈሣዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩና በአካባቢው እየተስፋፋና እያደገ የመጣው የመናፍቃን እንቅስቃሴ ሲሆን በዕለቱ TC Williams  በሚገኘው የመኪና ማቆሚያ ላይ 3 ሰዓት የፈጀ ውይይት ተደርጎ ለማኀበሩ ስያሜ በማውጣት እና የአገልግሎት ክፍሎችን በማቋቋም ተጠናቋል። በወቅቱ ረዥም ሰዓት የፈጀው ለማኀበሩ ስያሜ መስጠት ሲሆን 5  አማራጮች ቀርበው ከቀረቡት መካከል ምንም እንኳን ሁላችንም የተለያዩ ቅዱሰንን ብንወድም ሁላችንንም የሚያስማማን የእመቤታችን ስያሜ በመሆኑ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም  በስደት ለምንኖር አምባችን መጠጊያችን ስለሆነች ማኀበረ ጽዮን ማርያም በሚለው ጸንቷል።


የማኅበረ ጽዮን ማርያም ጉዞ

የማኅበሩን ጉዞዎች  አራት ገጽታዎች ነበሩት።

ማኅበሩ በእየሩሳሌም

የማኅበሩ ጉዞ በእየሩሳሌም የሚባለው ማኅበሩን በመሠረቱት 6ቱ አባላት መካከል ለ 4 ተከታታይ እሁዶች ስብሰባ እና ወይይት በማድረግ ለ2 ወር የማኅበሩን ደንብ፤አላማና የአገልግሎት ክፍሎች አዋቅሯል።

ማኅበሩ በይሁዳ

 የማኅበሩ ጉዞ በይሁዳ የሚባለው፣ሃይማኖታቸውን ለሚያውቁ፣ቤ/ን ለሚሄዱና ለመንፈሣዊ ነገር ቀና አመለካከት ያላቸውን ክርስቲያኖች  በመጥራት፤ የማኅበሩ አባል ሆነው የእመቤታችንን ፅዋ አብረው እንዲጠጡ በማድረግ የተሻለ ደንብ በማውጣት የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ እንዲደርስ ፤ገዳማትን በመርዳት ፤ነዳያንን በመመገብ ለሁለት አመት ቆይቷል

ማኅበረ ጽዮን ማርያም በሰማርያ

በወቅቱ በነበሩት የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቆዎስጦሰ መልካም ፍቃድና ቡራኬ፣ማኅበሩ አገልግሎቱን በግልጽ በ አመኑና ባላመኑ መካከል፣ በጉባኤ ደረጃ ማድረግ የጀመረበት ጉዞ ሲሆን በዚህ ጊዜ ቃለ እግዚአብሔር በሰፊው እንዲሰጥ በማድረግ ምዕመኑ ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ በማድረግና ገዳመትን በበለጠ መርዳትና ነዳያን ምገባ በማጠናከር ከ2 እሰከ 3 ዓመት ቆይቷል።

ማኅበረ ጽዮን ማርያም በመላው ዓለም

ማኅበሩ “በመላው ዓለም” የምንለው፣ከ15 ቀን ጉባኤ ወደ ቅድስት ቤ/ን ምስረታ የተሸጋገርንበትን ነው፣ በዚህ ጉዞ ማኅበሩ ወደ ቤተክርሲቲያን ማደጉ ሲሆን
በሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም አማካይነት ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤ/ን ከተተከለ በኋላ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በቤተክርስቲያን ደረጃ መስጠት ጀመረ። ከዚህ በኋላ ጽዮን ማርያም የሚለው ስያሜ ለሰ/ት/ቤቱ ተሠጠ። በጉዞአችን ሁሉ ከእኛ ጋር በመሆን ላገለገሉን አገልጋዮች ሁሉ እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛላችሁ፤ የአገልግሎት ዘመናችሁን ያርዝምላችሁ እንላለን።


(የደብሩ ሰንበት ት/ቤት የአንደኛ ዓመት ምሥረታ በዓሉን አስመልክቶ ካዘጋጀው መጽሔት የተወሰደ)